የዓሣ ምርምርና ትምህርት ማዕከል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የዓሣ ምርምርና ትምህርት ማዕከል ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት፣ ም/ፕሬዚደንቶች፣ ዲኖች፣ በዘርፉ የሚሳተፉ የሲዳማ ክልል ባለሙያዎች እና ዓሳ አርቢዎች ተሳትፈዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ኮሌጁ በዓሳ፣ በሰብልና አትክልት ብሎም በፍራፍሬ ምርት በሲዳማ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመቀየር በጥናት ምርምር የተደገፉ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለማስተዋወቅ እየሰራ ይገኛል። ፕሬዚደንቱ አክለውም ተፈጥሮ የለገሰችንን የውሀና የዓሳ ሀብት ልማት በአግባቡ በመጠቀም ከውጭ የሚገባውን የዓሳ ምርት በማስቀረት የሀገራችንን የአሳ ፍጆታ ከማሟላት ባሻገር በዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን የማስፋፋት ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመው ኮሌጁ በዚህ ዘርፍ ላይ እየሰራው ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንዲሄድበት አሳስበዋል።

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ በበኩላቸው የዓሳ እርባታ ምርምርና ትምህርት ማዕከል በ2007 ዓ.ም የተቋቋመና የዓሳ ምርትን ለማጠናከር፣ ጥራት ያለው የውሀ ሀብት አጠቃቀም ዘዴን ለመፍጠር እንዲሁም የእርሻ ምርትን ለማሳደግ ምርምሮችን በማካሄድ ሳይንሳዊ ምክሮችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዲኗ እየጨመረ የመጣውን የሰው ልጅ ቁጥርና ተያይዞ የሚከሰተውን ከፍተኛ የምግብ ፍጆታ ፍላጎት መጨመር ለማሟላት የምግብ አመራረታችንን ከባህላዊ የግብርና ስርዓት ወደ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ግብአቶች ማዘመን እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብትና በሥነ-ምህዳር አገልግሎቶች አስተዳደር ላይ በመመሥረት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከእንደዚህ ያሉ የምርምር ማዕከላት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓሳ እርባታ ምርምርና ትምህርት ማዕከል ኃላፊ ወ/ሮ ፌቨን ዘሪሁን የአውደ ጥናቱን ዋና አላማ ሲያስረዱ በአኳካልቸር ቴክኖሎጂ ውስጥ የተከናወኑ ለውጦችን በመገምገም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ያጋጠሙ ችግሮች ላይ መፍትሔ መስጠትና ለወደፊት በዘርፉ የሚደረጉ የምርምር ዘርፎችን በመለየት ለማሳደግ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ አብራርተዋል።

በሲ/ብ/ክ/መ የእንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ የአሳ ሀብት ልማት ባለሙያው አቶ ሸንኮሩ ሞርካ በበኩላቸው በክልሉ የዓሳ እርባታ በምግብ ይዘቱ፣ በስራ እድል ፈጣሪነቱና በገበያ አዋጭነቱ ተፈላጊ መሆኑን ጠቁመው  ክልሉ የዓሳ ልማት እምቅ አቅም ያለውና በአሁኑ ሰዓት በ19 ወረዳዎች ላይ የእርባታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ክልሉ በሀዋሳ እና አርበጎና የጫጩት ማባዣ ማዕከላትን ከፍቶ ለ 4 አሳ አስጋሪ ማህበራትና 9 ኢንተርፕራይዞች የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለባለሙያዎች የንድፈ ሀሳብና የክህሎት ስልጠና እንዲሁም የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብሮችን እያዘጋጀ እንዳለም አቶ ሸንኮሩ ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ተሳታፊዎች በኮሌጁ የሚገኘውን የዓሳ እርባታ ማዕከል የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et