ዓመታዊ የምርምር ግምገማ አውደጥናት ተካሄደ

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዓመታዊ የምርምር ግምገማ አውደጥናት አካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዓመታዊ የምርምር ግምገማ አውደጥናት በአንድ ጭብጥ-ተኮር እና 14 ዲሲፕሊነሪ ምርምሮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በአውደጥናቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ተወካዮች፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሰራተኞች፣ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮና የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካዮች ተሳትፈውበታል።

የሀ/ዩ/ም/ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ራህመቶ አበበ አውደጥናቱን ሲያስጀምሩ በመንግሥት በጀት ብቻ ድጋፍ የተደረገላቸው ከ460 በላይ ዲሲፕሊነሪ እና ቴማቲክ ምርምሮች ባለፉት አምስት አመታት በዩኒቨርሲቲው መካሄዳቸውን ጠቅሰው ከእነዚህም መካከል 103 ያህሉ በህ/ጤ/ሳ/ኮ መደረጋቸውን ገልጸዋል። ዶ/ር ራህመቶ በምርምር የተገኙ ውጤቶች ለሳይንሱ ማህበረሰብ እና ጉዳዩ ለሚመለከተው ሕብረተሰብ በአግባቡ መሰራጨት እና የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ የመንግስት የጤና ቢሮዎች ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ  አሳስበዋል።

የኮሌጁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዝናው ሰርሚሶ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከራስ አልፈው ለሌላ ለመትረፍና የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት እንዲችሉ ኮሌጁ በምርምር ስራዎች እያገዘና ድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው ወደ ራስ-ገዝነት በሚደረገው ሽግግር የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ዋናውን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

የኮሌጁ ጥ/ምር/ማ/አገልግሎት ዳይሬክተር ተ/ፕ ረቂቁ ፍቅሬ እንደተናገሩት ዓመታዊ አውደ ጥናቱ ዩኒቨርሲቲው በለያቸው የማህበረሰቡ ቁልፍ ችግሮች ላይ ተንተርሰው በዩኒቨርሲቲው መምህራን በ2015 ዓ.ም እና ቀደም ብለው የተሰሩ የዲሲፕሊነሪና የቴማቲክ ምርምሮችን ሂደትና ውጤት ለመገምገም መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የዚህን አመት አውደጥናት ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ምርምሩን ካካሄዱት ተመራማሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሀኪሞች መሆናቸውና ጤናና ጤና ነክ በሆኑ ዘርፎች ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት መካሄዱ መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለዋል።

የኮሌጁ የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ሁናቸው በየነ ደግሞ በዕለቱ የሚገመገሙት የምርምር ስራዎች በአንድ አመት ውስጥ የሚጠናቀቁ ዲሲፕሊነሪ እና ከአንድ እስከ ሶስት አመት የሚጠይቁ ጭብጥ-ተኮር (ቴማቲክ) የምርምር አይነቶች መሆናቸውን ገልጸው በግምገማው የሚነሱ ሀሳቦች ሁሉ እንደጠቃሚ ግብዓት እንደሚወሰዱ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎች በየአመቱ ተቋማዊ እንዲሁም በየሁለት አመቱ ደግሞ ሀገር አቀፍ የምርምር አውደጥናቶችን እንደሚያካሂዱና የዘንድሮው ሀገርአቀፍ አውደጥናት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስለሚዘጋጅ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም በዚሁ ግዜ ጠቁመዋል።

ከተጋባዥ እንግዶች የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር አቶ ሙንጣሻ ብርሐኑ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የምሁራን መገኛ እንደመሆናቸው የማህበረሰቡን ችግሮች በሳይንሳዊ ዘዴ ለመፍታት በርካታ ምርምሮችን እንደሚሰሩ አንስተው እኚህን የምርምር ግኝቶች በመጠቀም እንዴት የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ይቻላል የሚለውን ለመለየት ኢንስቲትዩቱ በቅርበት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et