የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሞዴል ት/ቤት ተማሪዎች የሜሪጆይ ኢትዮጵያ ማዕከልን ጎበኙ።
ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም የሜሪጆይ ኢትዮጵያ የሀዋሳ አረጋውያን ማዕከልን የጎበኙት የዩኒቨርሲቲው ማ/ብ ሞዴል ት/ቤት የሁ/ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ናቸው።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ በጉብኝቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የበጎ አድራጎት ስራ ሰው መሆንን ብቻ የሚጠይቅ እንዲሁም በተግባር ተገልጾ ሲታይ ደግሞ ለአእምሮ ሰላምንና እርካታን የሚሰጥ ነው ብለዋል። ዲኑ አክለውም የሞዴል ት/ቤቱ ተማሪዎች ት/ቤቱን ከተቀላቀሉ ገና አምስት ወራት ብቻ የተቆጠረ ቢሆንም በዚህ በራሳቸው ተነሳሽነት የበጎ አድራጎት ክበብ በማቋቋም ማንም ሳያዛቸው ይህንን ጉብኝት ማዘጋጀታቸው ምን ያህል በእውቀት እና በስነ-ምግባር የታነጹ መሆናቸውን ማሳያ ሆኖ እንደሚቀርብ ገልፀው ሌሎች ተማሪዎችም ይህንን ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሞዴል ት/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ማንደፍሮ በበኩላቸው ተማሪዎቹ እስካሁን ባላቸው ቆይታ በርካታ መልካም ተግባሮችን ሲከውኑ እንደቆዩ አስታውቀው በሜሪ ጆይ የአረጋውያን ማዕከል ጉብኝትም ተማሪዎቹ በአቅራቢያቸው ካለው ማህበረሰብ ጋር መልካም ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ብለው በማሰብ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ተማሪዎች በአካባቢያቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማወቃቸው ለችግሮች መፍትሔ ያበጁ ዘንድ ቁጭትን የሚፈጥርና በትምህርታቸው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ እንደሚያግዛቸው አቶ እሸቱ ጨምረው ገልጸዋል።
በሜሪ ጆይ ኢትዮጲያ የኢትዮጵያውያን ለኢትዮጽያውያን ዲፓርትመንት አስተባባሪ ወ/ሮ እመቤት ተሬሳ ለተማሪዎች አቀባበል ሲያደርጉ እንደገለፁት ድርጅታቸው ላለፉት ሰላሳ አመታት የልማትና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ መሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ሲሳተፍ የቆየ ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑን ጠቁመው ማዕከሉም በኢትዮጵያውያን ሀብት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሰባት አመታት ተቆጥረዋል ብለዋል። በማዕከሉ ለችግር የተጋለጡ ወላጅ አልባ ልጆችና አቅመ ደካማ አረጋውያን በቋሚነት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረው በዕለቱ ተማሪዎችና መምህራኑ እነርሱን ለመጎብኘትና ድጋፍ ለማድረግ በዚያ በመገኘታቸው ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
በመጨረሻም የሞዴል ት/ቤቱ ተማሪዎች ተወካይ የሆነችው ተማሪ ሀና ቦጋለ መልካምን ማሰብና ማድረግ የሁሉም ሰው ድርሻ መሆኑን እና ልጆች ነገ ላይ ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎች ለመሆን ዛሬ ላይ ህብረተሰቡን የሚጠቅሙና በታላላቆቻቸው የሚያስመርቃቸውን ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግራ ተማሪዎቹ ያሰባሰቡትን አልባሳትና ከኪሳቸው ቀንሰው ያዋጡትን ገንዘብ ለማዕከሉ ኃላፊ በማስረከብ ማዕከሉን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።