የአእምሮ ቀረፃ (mind set) ስልጠና ተሰጠ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ከብርሃን መንገድ ባለራዕዎቾ ማኀበር ጋር በመተባበር የአእምሮ ቀረፃ (mindset) ስልጠና ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ጥር 18/2016 ዓም ሰጥቷል።

በሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ም/ኘሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ ስልጠናውን ሲከፍቱ እንደገለጹት ተማሪዎች በዩኒቨረሲቲ ቆይታቸው ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ የወደፊት ሕይወታቸውን የሚመሩበትን ራዕይ ቀርፀው አስፈለጊ ቅድመ ዝግጅቶችን የሚጀምሩበት በመሆኑ የአቻ ተሞክሮዎች እና የስልጠና መድረክ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። እንዲህ አይነት ስልጠናዎች ተማሪዎችን በመልካም ስነ-ምግባር በማነጽ ከአቻዎቻቸው የተሻለ የሕይወት ተሞክሮዎችን በመቅሰም የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በብቃት እንዲወጡ ያስችላልም ብለዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መማክርት ኘሬዚደንት ተማሪ እሰይ ጴጥሮስ እንደገለፀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚመጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እርስበርሳቸው ከሚለዋወጡት ተሞክሮ በተጨማሪ ስኬታማ ወጣቶችን በመጋበዝ ተሞክሮዎቻቸውን እንዲያጋሩ እየተደረገ መሆኑን ገልፅዋል።

በመድረኩ ላይ ከቀረቡት ስራ ፈጣሪና ሰኬታማ ወጣቶች መካከል በቡና ምርት ማቀነባበሪያና ላኪነት የተሰማራ ወጣት ከነአን አሰፋ ዱካሞ እንዲሁም የቀድሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሕግ ባለሙያና ደራሲ ዳግማዊ አሰፋ የሕይወት ተሞክሮዎቻቸውን አቅርበዋል።

ወጣቶች በማኀበራዊ ሚድያ አጠቃቀም በተለይም ፌስ-ቡክ እና ቲክ-ቶከ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ በማስተዋልና በዕውቀት መሆን እንደሚገባውና ለሀገር የሚጠቅም ዕውቀትና ጥቅም በሚያስገኝ ጉዳይ ላይ ማትኮር እንደሚጠበቅባቸው ወጣት ከነአን አሰፋ ዱካሞ አስገንዝቧል።

የሕግ ባለሙያና ደራሲ ወጣት ዳግማዊ አሰፋ ከሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን በከፋተኛ ማዕረግ ጨርሶ ወደ ስራ በተሰማራ አጭር ጊዜ ውስጥ በድንገተኛ አደጋ ከፋተኛ የአካል ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ ሁለት መጽሐፎችን አሳትሞ ለአንባብያን ማብቃቱን ገልጿል።

በአደጋው ምክንያት እጅና እግሩ ሰለማይታዘዙለት በሰው ሠራሽ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ስራዎችን ለማከናወን ራዕይ እንዳለው ተናግሯል::

ከ1500 በላይ መደበኛ ተማሪዎች በኘሮግራሙ የተሳተፉ ሲሆን ከተማሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በተማሪዎች ከተነሱ ሃሳቦች መካከል ተመሳሳይ ኘሮግራሞች በዕረፍት ቀናት ቢካሄዱ የተሻለ ስብዕና ለመገንባት እና ስለ ሕይወት ጥሩ ግንዛቤ እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ይገኙበታል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et