በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሶስት ክልሎች የተውጣጡ 120 ባለሙያዎችን በከተማ መሬት ፕላን እና በከተማ ፋይናንስ ዘርፍ ለ45 ቀናት የሚቆይ ተግባር-ተኮር ስልጠናና ምዘና ለማካሄድ የማስጀመሪያ መርሃግብሩን ሚያዚያ 22/2018 ዓ/ም አካሂዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በዚሁ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ላለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ መሰል ስልጠናዎችን ለመስጠት ከኮሌጁና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመስራት የመረጠውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን እና ስልጠናውን በብቃት እየሰጠ ያለውን የወ/ደ/ተ/ሃ/ኮለጅ ከልብ አመስግነዋል:: ፕሬዝዳንቱ ለሰልጣኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት ይሄንን ሙያዊ ብቃታቸውን ከፍ የሚያደርግ የስልጠና ዕድል ተጠቅመው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ለሕዝብና ለሀገራችን ጥቅም የላቀ አበርክቶ እንዲያደርጉበት አሳስበዋል።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊና የመድረኩ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ዚነት ኢብራሂም በበኩላቸው የስልጠናና ምዘናው ዋና አላማን በማስመልከት ገለፃና የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል:: በንግግራቸውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀዋሳ ዩንቨርስቲን ጨምሮ በአምስት ዩንቨርስቲዎች ትብብር ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ እስካሁን 8000 ሙያተኞችን በማሰልጠን በስራው ላይ የተሻለ ተፅዕኖ መፍጠር እንደተቻለ ገልፀዋል:: ወ/ሮ ዚነት አክለውም አሁን ላይ ያለው የሃገራችን የከተሞች እድገት ደረጃ በዓለም አቀፍ መስፈርት ሲለካ ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ጠቁመው እየተስፋፉ ያሉት ከተሞቻችን በሙያ ካልተመሩ ተገቢውን ደረጃ መያዝ እና የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት ስለማይቻል ስልጠናና ምዘናው እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ አስምረውበታል።
የወ/ገ/ደ/ተ/ሃ/ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወ/አማኑኤል ኮሌጁ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የተደራጁ ቤተ ሙከራና ቤተ መፃህፍት፣ እንዲሁም ሰፊ የሙከራና ትግበራ የምስክ ትምህርት መስጫ ቦታ ይዞ የተደራጀ አንጋፋ ኮሌጅ በመሆኑ ሰልጣኞች ሙሉ ትኩረታቸውን ተጠቅመው በቆይታቸው መልካም ፍሬ ይዘው ለመመለስ ተግባራዊ ስልጠናቸውን በትጋት እንዲከታተሉ አደራ ብለዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የመሬት አስተዳደርና ቅየሳ ት/ክፍል ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ የሆኑት አቶ አባይ አስረስ ለሰልጣኞች ሙሉ የፕሮግራም ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ከሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለመጡት 120 ሰልጣኞች 70% የተግባር እና 30% የንድፈ ሃሳብ ይዘት ያለው ስልጠናና ምዘና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
