በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት አስተባባሪነት “የመንገድ ትራፊክ አደጋ፦ በኢትዮጵያ ችላ የተባለው ወረርሽኝ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከልና ሊወሰዱ በሚገባቸው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እርምጃዎች ዙሪያ በርካታ የዘርፉ ምሁራንና የጸጥታ አካላት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግንቦት 28/2018ዓ.ም ምክክር ተካሂዷል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ ከሆኑ ችግሮች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ከሚይዙት አንዱ የሆነው የትራፊክ አደጋ የሰው ልጅን ህይወት ከመንጠቅ ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን የሚፈጥር በመሆኑ እንዴት ከዚህ ችግር መላቀቅ እንደሚቻል መነጋገር ጊዜው የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። የትራፊክ አደጋ በርካታ ተዋንያንን የሚያሳትፍ በመሆኑ የመከላከል ስራውም የተሽከርካሪውን ደህንነት ከሚጠብቁ መካኒኮች ጀምሮ አሽከርካሪዎችን፣ እግረኞችን እና የህግ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ሊሰራ እንደሚገባው ም/ፕሬዚደንቱ ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምና ማህበር ፕሬዚደንት እና የመገጣጠሚያ አጥንት ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኤፍሬም ገብረሐና የትራፊክ አደጋን አለማቀፍና ሀገራዊ ተጽዕኖ በዳሰሱበት ጽሁፉቸው የመንገድ ትራፊክ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከየትኛውም ታዋቂ ተላላፊ በሽታ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሰው ላይ ሞትና የአካል ጉዳት የሚያስከትል አስከፊ ችግር ስለመሆኑ ጠቁመዋል። እንደ ኢትዮዽያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የሚመዘገበው የትራፊክ አደጋ መጠን ካለን የተሽከርካሪ ብዛት ጋር የማይመጣጠን መሆኑ ለአደጋው መከሰት ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት ማሳያ ተደርጎ ሊቀርብ እንደሚችል ዶ/ር ኤፍሬም ገልጸዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮ/ስ/ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ገብረዮሐንስ በበኩላቸው በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት ስለሚከሰቱ የአከርካሪ አጥንት ጉዳቶች እና ሞት ሳይንሳዊ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን አደጋዎቹን ቀድሞ ማስቀረትና መከላከል ጉዳቶችን የምንቀንስበት ዋነኛ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላው የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅራቢ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮ/ስ/ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ስንታየሁ ቡሳ በሲዳማ ክልል በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት ያለውን ተጨባጭ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ገጽታ በጥናታዊ ጽሑፍ ለተሳታፊው ያሳዩ ሲሆን፣ በክልሉ ያለውን ይኸንን አስከፊ ችግር በዘላቂነት ለመቀነስ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች መደረግ አስፈላጊ መሆናቸውን በጽኑ ተናግረዋል።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ደህንነት ትራፊክ አደጋ መከላከያ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መለሰ ቡኑራ በበኩላቸው በክልሉ በተለይም ከሞተር ብስክሌት ተሽከርካሪዎች ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ በቁጥሩም በአይነቱም ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ አጠቃላይ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥሩንና ደህንነቱን የማስጠበቅ ስራ ለማጠናከር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመጠቀም የተሻለ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
