በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2018 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያዉ መንፈቀ ዓመት በሙከራ ደረጃ በበይነ-መረብ በመታገዝ ለመጀመሪያ አመት የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ሲሰጡ የነበሩትን የሒሳብ ትምህርት እና Introduction to Emerging Technology ኮርሶች አፈጻጸም የገመገመ መድረክ በዩኒቨርሲቲዉ ኢ-ለርኒንግ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ሚያዝያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በቴክኖሎጂ ኢንሲቲትዩት ተካሄዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ ጌታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው መማር-ማስተማርን ይበልጥ ተደራሸ ለማድረግና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር ከተያዙ የትምህርት ዘርፍ ትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ለዜጎች መስጠት ነዉ ብለው ዲጂታል ቴክኖሎጂን ከመማር ማስተማር ሂደት ጋር ማስተሳሰር ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል:: ባለፈው መንፈቅ ዓመት የተጀመረው በበይነ-መረብ የታገዘ ትምህርት አሰጣጥ ሂደት ውጤታማነትን ለመለካት የባለድርሻ አካላት ዉይይት መድረክ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የቀጣዩ ጊዜ የትምህርት አሰጣጥ በተለምዶ ክፍል ዉስጥ ብቻ ከሚሰጠዉ ባሻገር ቦታና ጊዜ ሳይገድብ በበይነ-መረብ በመታገዝ እንደሚሰጥ እና ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ በእስካሁኑ ሂደት የታዩ ጠንካራ ጎኖችና በቀጣይ መስተካከል ያለባቸው ደካማ ጎኖች ላይ ሰፊ ውይይት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ፈንታሁን ሞገስ በበኩላቸው የትምህርት ስርዓቱን ለማዘመንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የትምህርት ይዘትን ከቴክኖሎጂ ጋር ማቀናጀት የግድ መሆኑን በመጥቀስ በኢንስቲትዩቱ በሙከራ ደረጃ ሲሰጥ የነበረው ኮርስ ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራኑ አዲስ ልምድ የሰጠ ሆኖ ማለፉን ገልጸዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢ-ለርኒንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ እንደተናገሩት በእነዚህ ኮርሶች አሰጣጥ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር በሚቀጥለው ዓመት በከፊል በበይነ-መረብ የታገዘ ትምህርት አሰጣጥን የበለጠ ለማስፋት መታቀዱን እና ለዚህም ይረዳ ዘንድ በዘጠኝ ተጨማሪ ኮርሶች ላይ የይዘት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዉይይት መድረኩ ላይ በበይነ-መረብ የታገዙ ኮርሶችን በማዘጋጀት እና በማስተባበር ሂደት ላይ በተሳተፉ መምህራን ጽሁፎች ቀርበዉ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በማጠቃለያው ላይ እንደተመላከተው የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና የመምህራንንና ተማሪዎችን አቅም በመገንባት በመጪው የትምህርት ዘመን በስፋት ወደ ስራ ለመግባት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
