በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በከተሞች ኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ንድፈ-ሀሳብና ተግባር ላይ ያተኮረ ሴሚናር ሚያዚያ 24/2018 ዓ/ም አካሂደዋል።
የሀ/ዩ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ፕላንና አርኪቴክቸር በርካታ ምሁራንን እያሰለጠነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዘመናዊ የከተሞች ዕድገትና አወቃቀር ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በስፋት እያካሄደ ይገኛል። የሴሚናሩ ዓላማም በሀገራችን የከተሞች ዕድገት ዘላቂ ልማት ለማምጣት ከዋነኞቹ አስቻይ ዘርፎች አንዱ እንደመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆት እያተረፈ ያለውንና ሐዋሳን ጨምሮ በሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች እየተስፋፋ የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ንድፍ -ሀሳብ እንዲሁም ተግባራትን በመፈተሽ ተመራማሪዎቹ በሀዋሳ ከተማ ከተጀመረው የኮርደርና ሃይቅ ዳርቻ ልማት ጋር እንዲያስተሳስሩ አቅም ለመፈጠር መሆኑን ዶ/ር ታፈሰ ገልፀዋል።

የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የውሃ ሃብትና አካባቢ ምህንድስና ተመራማሪና ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት ደናንቶ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ በ3ኛው ምዕራፍ ለማካሄድ በታቀደው የሃይቅ ዳር ኮሪደር ልማት ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ በዩኒቨርስቲው የሚገኙ የዘርፉ ምሁራን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ከተማ አስተዳደሩ ባስተላለፈው ጥሪ መነሻነት ምሁራን ተገናኝተው እንዲመክሩበት መድረኩ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስትራቴጅክ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የቀድሞ የሀ/ዩ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ኢ/ር እሽታየሁ ክንፉ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች በንድፈ-ሃሳብና ትግበራ መካከል በነበሩ መስተጋብሮች ምክንያት የተፈጠሩት የዕውቀት ሽግግሮች ላይ ያተኮረ ሰፊ ትንተና አቅርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል።
ለግማሽ ቀን በተካሄደው ፕሮግራም ተማሪዎች : መምህራን : ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል።
