ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ ዕቅድ አፈፃፀሙን እና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅዱን የገመገመበት የካውንስል ውይይት መድረክ ነሐሴ 14/2018 ዓ/ም በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በነበረው የሥራ እንቅስቃሴ በርካታ ተደራራቢ ሥራዎች፣ ውስብስብ ሁኔታዎችና ሃገራዊ ግዴታዎች በነበሩበት ሁኔታ ውስጥ አልፎ አመርቂና ስኬታማ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመው የዩኒቨርሲቲውን መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ የታመነበት የራስገዝነት ሽግግር የዝግጅት ዶክመንት (Autonomous Transition Documents) ተዘጋጅቶ ለትምህርት ሚኒስቴር መላኩን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ በነበሩት የትምህርት፣ የምርምርና የማህበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች አፈፃፀም ላይ የተማሪዎች የመውጫ ፈተና ዝግጅትና ውጤት፣ የምርምርና ህትመት እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ስራው መልካም አፈጻጸሞች የታየበት እንደነበር ፕሬዚደንቱ አክለዋል።

በዕለቱ የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና ትብብር፣ እንዲሁም የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚደንቶች እና የዩኒቨርሲቲው ገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ የየዘርፋቸውን ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም፣ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመሻገር የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲሁም በአዲሱ በጀት ዓመት ሊሰሩ ያቀዷቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች የያዘ ሪፖርት ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አቅርበዋል።
ሪፖርቶቹ ከቀረቡ በኋላ ከዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት በርካታ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና የማሻሻያ ጥቆማዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይም ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክፍተቶች፣ የአሰራርና አስተዳደር ማስተካከያዎች እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ግልፅ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ማጠቃለያም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ፤ ያጋጠመውን የበጀት እጥረትና የግብዓት ክፍተቶች ለመቅረፍ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፣ አሰራርን ማዘመን፣ እና በ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት ሙሉ አቅምን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
