የሲዳማ ብ/ክ/መ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማስፋፊያ በ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ የተሰሩ 6 ፕሮጀክቶችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል::
ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት ፕሮጀክቶች ልዩ የቀዶ ሕክምናና የወሊድ ፅኑ ህሙማን ክፍል፣ የክሊኒካል ሙከራ ማዕከል (Clinical Trial Unit)፣ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና የልህቀት ማዕከል፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጡት ወተት ባንክ፣ የኦክሲጅን ማምረቻና የሕክምና ጋዝ ሥርዓት፣ እና የሕክምና ቆሻሻ ማቃጠያ (Incinerator) ናቸው::
ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው ወቅት እንዳሉት፥ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው አበረታችና ወጪ ቆጣቢ ውጤት የተቋሙን ትልቅ አቅም የሚያሳይ ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የጤና አገልግሎትን ለማስፋፋት፣ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅና ጥራት ያለው ሕክምና ለማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ገልጸው የክልሉ መንግስት አስፈላጊ በሆኑ ዘርፎች ለበለጠ ስኬታማ ሥራ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለሕዝቡ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አመልክተው የጤና ሥርዓቱ ከሕክምና አገልግሎት ባሻገር በሽታን በመከላከል፣ በምርምር፣ በእናቶችና ሕጻናት ጤና እንዲሁም በአካባቢ ጤና ጥበቃ ዘርፎች ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያሰራቸው ፕሮጀክቶች በዚህ ረገድ የህክምና አገልግሎትን፣ የህክምና ትምህርትና የጤና ምርምርን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ገልፀው የህክምና ባለሙያዎችም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተሟላበት ተቋም ውስጥ ማገልገል ስኬታማና የሚያረካ ሥራ እንዲሰሩ ያግዛል ብለዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በበኩላቸው ይሄንን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ ድርሻ የነበራቸውን ዓለም አቀፍ እና የሃገር ውስጥ አጋሮች እንዲሁም በትጋት ሲያገለግሉ የቆዩ የኮሌጁ አመራርና ሐኪሞች ልባዊ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም የበለጠ ትብብርና አበርክቶ እንደሚኖር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል::
የኮሌጁ ቺፍ ኤክሰኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍፁም ወ/ገብርኤል በበኩላቸው የተሰሩ ፕሮጀክቶች ለዘርፉ ያላቸውን የላቀ አስተዋፅኦ ዘርዝረው ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል::
በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ጥራቱ በየነን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል::
/im