የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ባለስልጣን እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “ማንበብ ብቁ ሰው ያደርጋል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለ የንባብ ሳምንት የመክፈቻ ፕሮግራም የሲዳማ ክልል፣ የባለሥልጣኑ እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲያን እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ መስቀል አደባባይ በድምቀት ተካሂዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢ/ር ፍስሃ ጌታቸው በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ለማክበር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ እንደሆነ ጠቁመው እስካሁን ከ120 ሺህ የሚበልጡ ምሁራንን ያፈራ የእውቀት ተቋም እንደመሆኑ የንባብ ባህል እንዲጠናከር ከሚሰራው ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፃህፍት ጋር ይሄንን ፕሮግራም በማዘጋጀቱ ደስተኛ እንደሆነ ገልፀዋል::
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬስብሀት በበኩላቸው የንባብ ሳምንትን ዓላማ ሲያብራሩ መስሪያ ቤታቸው ለንባብ መዋል የሚችሉ መጽሐፍትን የማሰባሰብ፣ የተሰባሰቡትን በቤተ-መጽሐፍትና ቤተ-መዛግብት ዘመናዊ በሆነ መልኩ ማደራጀት እንዲሁም ከትምህርት ተቋማት እና የመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር የንባብ ባህልን የማዳበር ስራ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው ንባብ እውቀትና መረጃን ከማስጨበጥ ባሻገር ስብዕናን እና አሰላሳይነትን በማሳደግ የተሟላ ማንነት እንደሚገነባ እንደመሆኑ ትውልዱን ወደ ንባብ ባልህ እንዲመጣ ለማነሳሳት ነው ብለዋል::

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር እሺኔ ሐንቃሎ ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት የሲዳማ ብሔር እንደሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች ሁሉ የራሱ ባህልና ታሪኮች ያሉት መሆኑን ገልጸው ይህንኑ ሀብት ወደቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በጽሑፍ የመሰነድ እና በበቂ ሁኔታ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ በርካታ ምሁራን የንባብ ጠቀሜታን በተመለከተ የራሳቸውን የሕይወት ተሞክሮ እና ምሁራዊ ሀሳቦቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኢትዮዽያ ሳይንስ አካዳሚ ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ኢትዮዽያ የረዥም ጊዜ የስነ-ጽሑፍ ታሪክ ያላት ሀገር በመሆኗ ይህንን የታሪክ ሀብት የሀገር ብሔራዊ ማንነት ማከማቻ በሆኑት ቤተ-መዛግብት እና ቤተ-መጽሓፍት የእውቀት ቅርሶቻችንን መጠበቅ እንዲሁም ለተመራማሪዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ንባብና የዲጂታል ዘመን እድልና ፈተናዎች ላይ አተኩረው የተናገሩት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መልሰው ደጀኔ በበኩላቸው ንባብ ከአዕምሮ እድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው በመግለጽ የዲጂታል ዘመን የመረጃ ፍሰትና ተደራሽነትን ማስፋቱ አዎንታዊ ቢሆንም የንባብ ትኩረትን በመቀነስ ደግሞ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አንስተዋል።
አንጋፋው ደራሲ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ በበኩላቸው በጠቅላላው ሲታይ የማንበብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን መታዘባቸውን ገልጸው መሰል መርሐ-ግብሮች መነቃቃትን ለመፍጠር በተከታታይነት ሊከወኑ ይገባል ብለዋል።
