በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ መቀጠር: የሥራ ፈጠራ ማጎልበቻና የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል በ2019 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎችን ጨምሮ ማዕከሉ ለሁሉም ተማሪዎች የሚሰጣቸውን ተከታታይ የሙያና ክህሎት ስልጠናዎች ያስተዋወቀበት እና የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች የነበሩ ሁለት ስኬታማ መምህራን የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉበት ታላቅ የማነቃቂያ መድረክ ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሂዷል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ ጌታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚያገኙት የቀለም ትምህርት ባሻገር ከሰዎች ጋር ተግባብቶና አብሮ የመኖር አቅም የሚሰጡ የህይወት ክህሎቶችን በማዳበር የተሟላ ስብዕና ሊላበሱ እንደሚገባ በመግለጽ በዚህ ረገድ ማዕከሉ የሚሰጣቸው ተከታታይ ስልጠናዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙባቸው አሳስበዋል።
የመቀጠር ምጣኔ ማጎልበቻና የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተሩ አቶ ክብረት ፈቃዱ በበኩላቸው ማዕከሉ በ2012 ዓ.ም ተቀያያሪ ባህሪ ያለውን የስራ አለም በተመለከተ ለተማሪዎች ተፈላጊውን እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ታልሞ ስራ የጀመረ መሆኑን አስታውሰው በዋናነት በስራ ፈጠራ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ተማሪዎች የክህሎት ስልጠናና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ተቀጥረው መስራት ለሚፈልጉ ደግሞ ከቅጥር ዝግጁነት አንስቶ ከአሰሪዎች ጋር የማገናኘት ስራ ጭምር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ትምህርት የማያልቅ የህይወት ጉዞ በመሆኑ ሁልጊዜም እራስን ለአዳዲስ እውቀቶች ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ፕሬዚደንት ተማሪ ቢንያም አየለ በዚህ ረገድ ተማሪዎች በተለያዩ ክበባት ውስጥ መሳተፍ እንዲሁም ማዕከሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በፍላጎት መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ በመገኘት ለተማሪዎች የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉት መምህርት እና የዩኒቨርሲቲው የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ "ከተማሪነት እስከ መሪነት - የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የሕይወቴን አቅጣጫ እንዴት እንደቀረፀው" በሚል ርዕስ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉበት እና ወደ ስራው አለም የገቡበት እንዲሁም በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉበት ማንነት እንዲኖራቸው በተማሪነት ዘመናቸው እንዴት መስመር እንደያዘ አስረድተዋል:: ዘመኑ የቀለም እውቀት ብቻ የማይበቃበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ልዩ ክህሎት ለማዳበር በርካታ ዕድሎች ያሉበት መሆኑን በመገንዘብ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ዛሬ ላይ ሆነው የነገ ማንነታቸውን መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዩኒቨርሲቲው በመምህርነትና በሥራ ፈጠራ አሰልጣኝነት የሚያገለግሉት እንዲሁም የራሳቸውን የግል ሥራ የፈጠሩ ሆነው የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉት አቶ አባተ ኃይሉ ለተማሪዎቹ ከሕይወት ተሞክሯቸው በሰፊው አካፍለዋል:: መምህር አባተ ዲግሪያችሁ ብቻውን የተረጋጋና መሰረታዊ ዋስትና ያለው ሕይወት እንዲሰጣችሁ ሳትጠብቁ ራሳችሁን በክህሎት እና የሥራ ፈጠራ አብቁ በማለት የማነቃቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል::
በመጨረሻም ሁለቱ መምህራን ከተማሪዎች የቀረቡላቸው በርካታ ጥይቄዎችን ተቀብለው ያብራሩ ሲሆን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በርካታ የሕይወት ክህሎቶችን አዳብረው ለመመረቅ ጠቃሚ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ጥቆማ ተሰጥቷቸው መድረኩ ተጠናቋል::
