Skip to Content

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ሲዳማ ልማት ማህበር በቡና የእሴት ሰንሰለት እና ምርታማነት ማሳደግ ላይ የሚያተኩር የትብብር ፕሮጀክት ለመተግበር ስምምነት ተፈራረሙ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ልማት ማህበር  ጋር በመተባበር በሲዳማ ክልል የቡና አርሶ አደሮች ምርታማነትንና ጥራትን በምርምርና በቴክኖሎጂ ለማሳደግ የሚያስችል የአምስት ዓመት (2019-2023 እ.ኢ.አ) የትብብር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርመዋል።


በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተዉ መልዕክት ያስተላለፉት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ፣ ኢትዮጵያ የቡና ምርት መገኛ ከመሆኗ ባሻገር በዓለም አቀፍ ግብይት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት ዋና ምርት በመሆኑ፣ የቡናን ምርታማነትና ጥራት በምርምርና በቴክኖሎጂ ድጋፍ ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይህ የፕሮጀክት ስምምነት በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን አጋርነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ ደረጃ በማሳደግ በክልሉ ዘላቂ ልማት  ለማምጣት ጉልህ ድርሻ ያለዉ መሆኑን አብራርተዋል።

የሲዳማ ልማት ማህበር (ሲልማ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ክብርት ወይንሸት መንገሻ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ባለፉት 30 ዓመታት በክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀው፣ በሁለቱ አጋር አካላት በቀጣዮቹ ዓመታት የሚተገበሩ 5 ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ አርሶ አደሮችና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።


የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ ፊታሞ በበኩላቸዉ፣ ዞኑ በክልሉ ውስጥ በቡና ምርትና ጥራት የተሻለ ደረጃ ላይ ከሚገኙ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ፕሮጀክት የአርሶ አደሩን፣ የልማት ሰራተኞችንና የባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት በመገንባት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረዉ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በመድረክ ላይ የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎችና የዞን አመራሮች ተገኝተዋል።

Share this post
Tags
Archive
College of Agriculture Organizes Technical Meeting with Nestlé Foundation at College of Agriculture