ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል አከባበር በይፋ ለመጀመር መዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ አመራሮች የበዓሉን አከባበር ከሚያስፈጽመዉ ዐቢይ ኮሚቴ ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ/ም ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ገልጸዋል::
በዚህ ስብሰባ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታዉ አየለ ለዐቢይ ኮሚቴዉ የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ክብረ-በዓሉ የዩኒቨርሲቲዉን የግማሽ ምዕተ ዓመት ረጅም ጉዞና ደማቅ ታሪክ በሚያጎላና አሁን የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳይ እንዲሁም የወደፊት አቅጣጫዉን በሚጠቁም መልኩ ይከበራል ብለዋል:: ይህንንም ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዉ ያለዉን አቅም፣ የሚመለከታቸዉን ባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጭምር በማስተባበር ይህንን መልካም አጋጣሚ ለዩኒቨርሲቲዉ ሃገራዊና አለምዓቀፍ ተልዕኮዎች መሳካት ያዉለዋል ብለዋል::

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዛሬ 50 ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የተከፈተው የግብርና ኮሌጅ ከሌሎች ኮሌጆች ጋር ተጣምሮ የፈጠረው፣ ዩኒቨርሲቲ ከሆነ በኋላ ብቻ ከ120 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀ፣ ከ40ሺ በላይ የምርምር ዉጤቶችን በማሳተም ለአለም የሳይንስ ዕውቀት ያበረከተ፣ ለበርካታ ሚሊየኖች በበርካታ ዘርፎች ሙያዊ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን የሰጠ፣ እና ከበርካታ አለምዓቀፍ ባለድርሻ እና ተባባሪ አካላት ጋር ዘመናትን ያስቆጠረ ስትራቴጂያዊ ትብብር መፍጠር የቻለ የሃገራችን አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነዉ::
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና ትብብር እንዲሁም የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝዳንቶች በበኩላቸው ጽ/ቤቶቻቸዉ የበዓሉ አከባበር ሥነ-ስርዓት በተሳካ ሁኔታ ይጠናቀቅ ዘንድ ከዐብይ ኮሚቴዉ ጎን በመሆን አስፈላጊዉን አስተዳደራዊ፣ የቁሳቁስና ፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል::
የዐብይ ኮሚቴ አባላቱም የተሰጣቸዉን ታሪካዊ ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ያላቸዉን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ገልጸዉ፣ ተልዕኮዉን ለመፈጸም አስፈላጊ ናቸዉ ያሏቸዉን ሀሳቦች ለከፍተኛ አመራሩ ያቀረቡ ሲሆን፣ አዎንታዊ ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል:: በዉይይት መድረኩ እንደተገለጸዉ የበዓሉ አከባበር ሶስት ምዕራፎች ያሉት ሲሁን የመጀመሪያዉ ምዕራፍ በጥቅምት ወር 2019 ዓ/ም አጋማሽ ላይ የሚከናወነዉ ይፋዊ የበዓል አከባበሩ መርሃ-ግብር ማብሰሪያ መድረክ ሆኖ በዓሉ በ2019 ዓ/ም ዓመቱን በሙሉ የሚከበር ይሆናል ተብሏል፡፡
የምስረታ በዓሉ አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ሆኖ ከሰባቱም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶችና ኮሌጆች የተወጣጡ 19 የአካዳሚክና የአስተዳደር ሰራተኞችን እንዲሁም የተማሪዎች ተወካይ የተካተቱበት ሲሆን በስሩ ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎችን ይዞ የተዋቀረ ነው፡፡
