Skip to Content

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ልማት ማህበር ጋር የእንሰት ሰብል ጥበቃ፣ ምርምር እና ስልጠና ማዕከል ምስረታ የትብብር ስምምነት ውል ተፈራረመ፡፡

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር በደቡባዊ ሲዳማ ዞን በሁላ ወረዳ ላይ የእንሰት ሰብል ጥበቃ፣ ምርምር እና ስልጠና ማዕከል ለማቋቋም ሐምሌ 20/2018 ዓ/ም የትብብር ስምምነት ውል ተፈራርሟል፡፡


በፊርማ ስነስርዓቱ ለይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ወይንሸት መንገሻ እንደገለጹት የሲዳማ ልማት ማህበር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ አኗኗር ለማሻሻል ላለፉት 30 በላይ ዓመታት በጥናት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በሂደትም በጥናት በተለዩ ስድስት ዘርፎች ላይ የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለ ማህበር ነው ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ወይንሸት አክለውም እንሰት በሀገራችን ከ25 ሚልዮን በላይ ሕዝብ ለምግብነት ብቻ ሳይሆን ለሁለገብ አኗኗሩ የሚደገፍበት ሃገርበቀል ሰብል መሆኑን አንስተው ይሄንን ሁሉ ሰፊ ማህበረሰብ የተሸከመ ቢሆንም በሰብሉ ዙርያ በቂ ምርምር ተደርጎ ምርታማነትና ጤናማነቱን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሥራ ለመስራት ከአንጋፋው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሸለ አጋር ባለመኖሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመስራት ታቅዶ ወደ ስራ ለመግባት ጫፍ ላይ በመድረሳችን እጅግ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በበኩላቸው በእንሰት ሰብል ዙርያ ያለው ችግር ከዝርያው መመናመን አንስቶ ሰብሉ ላይ አሁን ከሚታየው የመጥፋት አደጋ ለመታደግ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በላይ ቁልፍ ባለድርሻ አለ ብዬ አላምንም ብለዋል:: እንሰት ድርቅ በቀላሉ የማያጠቃው፣ ከስሩ ጀምሮ አንድም የተክሉ ክፍል ጥቅም ላይ የማይውል የሌለው፣ ከሰው ምግብነትና መድሃኒትነት እስከ መጠለያ መስሪያ እና የእንስሳት ምግብነት ሰፊ ጠቀሜታ የሚሰጥ፣ የሚሊዮኖችን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ በመሆኑ ዝርያዎቹን ከመጥፋት ለመታደግ ብሎም የተመረጡ ዝርያዎችን የሚያጠቁ በሽታዎችን ለመለየትና በምርምር የተለየ በሽታ የመቋቋም አቅም ለመፍጠር እንደዚሁም ከመሬት ጥበት ጋር ተያይዞ የመጣው የከብቶች ቁጥር መመናመን ለእንሰት በጣም አስፈላጊ የሆነውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማሳጣቱን ታሳቢ በማድረግ ተተኪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጭምር ለመስራት ዩኒቨርሲቲው ከማህበሩ ጋር በትብብር ለመስራት በቂ ሃብት መመደቡን ዶ/ር ታፈሰ ገልፀዋል:: ከዚህ በፊት በአንጋፋው የግብርና ኮሌጅ ምሁራን ከ30 ዓመታት በላይ በእንሰት ላይ ብዙ የምርምር ውጤቶችን በማሳተም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ ተቋም ቢሆንም ስራዎቹ በአንድ ላይ ተሰብስበው ወደ ፖሊሲ ለውጥና ትግበራ አለመለወጣቸውና በተበጣጠሰ መልኩ መሰራቱን ጠቁመው የዚህ ማዕከል ምስረታ ይሄንን ችግር በመቅረፍ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመስራት ዕድል ይሰጣል ብለዋል፡፡ ም/ፕሬዝዳንቱ በሲዳማ ክልል ሁላ ወረዳ የሚቋቋመው የእንሰት ጥበቃ፣ ምርምርና ስልጠና ማዕከል ለመነሻ የሚሆን ከኖርዌይ መንግስት (ICP V Project) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚጀመር ቢሆንም የማዕከሉን ዘለቄታዊ ስራ ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲው በራሱ መደበኛ በጀት የሚያስቀጥለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡


ስለ ሲዳማ ልማት ማህበርና ስለ ትብብሩ አጠር ያለ ገለጻ ያቀረቡት አቶ ግሩም ሽኒቴ የእንሰት ተክል የሲዳማ ክልልን ጨምሮ በሰፊው የደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍል ህዝቦች ዘንድ እንደዋና ሰብል የሚመረት እና በተለይም ሲዳማ የእንሰት መገኛ ምድር እንደመሆኑ ሰብሉን ከጥፋት ለመታደግና የህዝቡን ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሲዳማ ልማት ማህበር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ይሄንን ወሳኝ የትብብር ፕሮጀክት ማስጀመሩ እጅግ ወሳኝ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ግሩም እንዳሉት የማህበሩ የድጋፍ ድርሻ በየጊዜው የሚያድግ ሆኖ አሁን ላይ አንድ አራተኛውን ወጪ የሚሸፍን ሲሆን ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሶስት አራተኛውን (75%) የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የትብብር ፕሮጀክቱ በዝርያ ጥበቃ (landrace conservation)፣ አሳታፊ ምርምር (participatory research)፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ (youth employment and farmers associations)፣ እና የአቅም ግንባታ ሥራ (capacity building for community through training and knowledge sharing) በሚሉ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጽዋል፡፡


በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና የግብርና ኮሌጅ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች፣ የሲዳማ ልማት ማህበር አመራሮች፣ የደቡባዊ ሲዳማ ዞን እና የሁላ ወረዳ አስተዳደሪዎች ተገኝተዋል፡፡

Share this post
Tags
Archive
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የኩላሊት እጥበት ማዕከል አስጀመረ።