Skip to Content

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የኩላሊት እጥበት ማዕከል አስጀመረ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (ህ/ጤ/ሳ/ኮ) "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል የሚከናወነውን የ2018 ዓ/ም ሃገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ በሚገኘዉ ሜሪጆይ የኩላሊት እጥበት ማዕከል አካሂዷል።


"የላቀ የኩላሊት ሕክምና ለጤናማ ማህበረሰብ!" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው መርሃግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የህ/ጤ/ሳ/ኮ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍጹም ወ/ገብርኤል ኮሌጁ ሀገራዊ ተልዕኮዉን በመቀበል በየዓመቱ መሰል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለአካባቢዉ ማህበረሰብ በስፋት እንደሚሰጥ ጠቅሰዉ፣ በ2017 ዓ/ም በተከናወነዉ መሰል ስራ ኮሌጁ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች መካከል ከቀዳሚዎቹ ሶስት ሆስፒታሎች አንዱ በመሆን ዕዉቅና እና ሽልማት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሯ ለዚህ ስኬት የጀርባ አጥንት የሆኑትን የኮሌጁን ሀኪሞች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ አመራሮች፣ የድጋፍ ሰራተኞች፣ አጋር ተቋማትና ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት አመስግነዋል። ዶ/ር ፍፁም በንግግራቸው የኩላሊት ህመም በሕክምናው ዓለም 'ድምፅ አልባው ገዳይ' የሚል መታወቂያ እንዳለው ጠቅሰው አብዛኛው ታካሚ ህመሙ እንዳለበት ሳያውቁ ለከፍተኛ ጉዳትና የሕይወት ማጣት እንደሚዳረጉ በመረጋገጡ አገልግሎቱ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ፣ ምርመራና ልየታ እንዲሁም ነፃ ህክምና መስጠትን እንደሚያካትት ገልፀዋል።



የዘንድሮውን መርሃ-ግብር በይፋ ያስጀመሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታዉ አየለ ትብብር ለሰዉ ልጆች በተፈጥሮ የተቸረ ስጦታ መሆኑን አዉስተዉ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክሮ እደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አካላት ለማዕከሉ ዉጥኖች እንደ ዜጋና እንደ ማሕበረሰብ አካልየሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።


በመርሃግብሩ ላይ ስለ ኩላሊት ህመም ባህርያት፣ አጋላጭ ሁኔታዎች፣ የመከላከያ መንገዶች እና የህክምናውን ባህሪ በተመለከተ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የኩላሊት ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ትዕግስት ተስፋዬ ሰፊ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኩላሊት እጥበት ተጠቃሚዎች ለቲቢ በሽታ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ስለሚሰጠው ሕክምና ደግሞ በኮሌጁ የሳምባ ሰብ-ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ታሪኩ ተስፋዬ ለታዳሚዎች ሰፊ ማብራሪያ እና ሙያዊ ምክር ሰጥተዋል።


ዩኒቨርሲቲው ለሜሪ ጆይ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ለ80 ታካሚዎች ለሶስት ወር የሚሆን የቲቢ መከላከያ መድሃኒት የለገሰ ሲሆን 40 የሚሆኑ የኮሌጁ ሰራተኞች ደግሞ በክረምቱ የበጎ ፈቃደኝነት በነፃ አገልግሎት ለመስጠት ቃል እንደገቡ ተገልፅዋል። ከዚህ በተጨማሪ የኮሌጁና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት በበጎ ፍቃደኛነት በነቂስ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።


በመድረኩ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርዳቸዉ አናቶ በበኩላቸው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰቡ ዘንድ እያከናወናቸዉ ያሉትን መደበኛ የሆኑ እና የክረምት በጎ ፈቃድ ሰፋፊ የህክምና አገልግሎቶችን አድንቀዉ በዘርፉ መምሪያቸዉ በትብብር ለመስራት ያለዉን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።


የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲ/ር ዘቢደር ዘዉዴ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ለሜሪጆይ ኩላሊት እጥበት ማዕከል እያበረከቱት ያለዉን ሁለንተናዊ ድጋፍ አድንቀዉ፣ የኩላሊት በሽታ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና በርካታ ዜጎችና ቤተሰቦችን ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያዳረገ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠዉና በትብብር ሊሰራ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


በመርሃግብሩ የተገኙ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አካላት የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኩላሊትና ሳምባ ምርመራ እና ደም ልገሳ አከናዉነዋል:: የማዕከሉ አባል ለመሆንም ተመዝግበዋል።


በ2018 ዓ/ም የክረምት በጎ ፈቃድ ህክምና እና ጤና አገልግሎት ከ129 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በተመረጡ የጤና ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ነጻ የምርመራ እና ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን በመርሃ-ግብሩ ተገልጿል።

Share this post
Tags
Archive
American Space Hawassa Officially Inaugurated