ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም ጉዞ እና የራስ-ገዝነት (Autonomy) ሽግግር ልምድ ለመቅሰም ያለመ የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲኒቨርሲው የራስ-ገዝነት ሽግግር ግብረ-ኃይል አባላትና የዩኒቨርሲቲው ምክር ቤት (University Council) አባላት ማለትም ዲኖች፣ ዳይሬተሮችና በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት መድረክ ሰኔ 2/2018 ዓ ም በአፍርካ ህብረት አደራሽ ተካሂዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ስለ ውይይት መድረኩ ዓላማ ሲናገሩ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን የራስ-ገዝነት የሽግግር ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ እና እስካሁን 60 የሚጠጉ ሰነዶችን ያዘጋጀው ታስክ ፎርስ ሰነዶቹን ለማጽደቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቁን ጠቁመው ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮዎችን የመቅሰም ዕድል ስራዎቹን እንደሚያጠናክር ስለ ታመነበት መሆኑን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ በዝርዝር ያቀረቡት በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ሃላፊው ፕሮፌሰር ማቲዎስ ኢንሰርሙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ-ገዝ አስተዳደር (Autonomy) ሲሸጋገር የሄደበት መንገድ፣ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶችና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን አንስተዋል:: ፕ/ር ማቲዎስ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ-ገዝነት ለመሸጋገር ያደረጋቸውን ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች፣ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅትና የተቋማዊ አወቃቀር ለውጦችን በዝርዝር አብራርተዋል። በተለይም የራስ-ገዝ ሽግግሩ የዩኒቨርሲቲውን አካዳሚያዊ ነፃነት ለማረጋገጥ፣ የውስጥ ገቢን በራስ አቅም ለማሳደግና የአስተዳደር መዋቅሩን ለማዘመን ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ ይህንኑ ውጤታማ ለማድረግም የሰው ኃይል ልማትን ማጠናከርና ጠንካራ የባለድርሻ አካላት ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።
በመጨረሻም፣ በቀረበው ሰነድና የሪፎርም ተሞክሮ ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይትና ማብራሪያ ተደርጎባቸዋል።
ከተሳታፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ችሮታው የዩኒቨርሲቲው አመራር እና አጠቃላይ ማህበረሰብ እስካሁን በዝግጅት ላይ ያሉት ሰነዶች ለሚመለከተው አካል ቀርበው ከፀደቁ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሽግግር ግዜ እንደሚገባ ገልፀዋል:: የዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝነት አሁን ላይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የፖሊሲ አካል እንደመሆኑ የዩኒቨርሲቲውን ተቋማዊ ልማትና የንብረት አስተዳደር ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዱ የኢኮኖሚ ዝግጅቶችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ፕሬዝዳንቱ በማሳሰብ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል::
