የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓም ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ነው።
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመሰብሰብያ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል::
እስከ ነገ የሚቀጥለውን የውይይት መድረክ የከፈቱት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ሲናገሩ በተለይ መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች ላይ የበለጠ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል:: ፕሬዚደንቱ እንዳሉት ከተለመዱ የአፈፃፀም ሪፖርት ግምገማዎች ወጣ ብለን በተለይ የመውጫ ፈተናን እንዲሁም ውጤትን ማዕከል ያደረገ የዕቅድ አፈፃፀም እና የተሻለ የሪፖርት ዝግጅትና አቀራረብ ላይ እናተኩራለን ብለዋል::
በማስከተልም እስካሁን ድረስ በዩኒቨርሲቲያችን የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ተግዳሮቶች በጋራ በመስራት በጥንካሬ የመወጣት ልምዱ እንዳለን አይተናል እና አሁን ደግሞ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በሚያስችለን ሽግግር ወቅት ላይ እንደመሆናችን በጣም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል:: "ዘንድሮ ባለው የወቅታዊ ጉዳዮች መደራረብ የተነሳ ይሄንን መድረክ ለማዘጋጀት ራሱ ካለፈው ሳምንት ወደዚህኛው ለማምጣት ተገደናል:: ሆኖም ግን አሁን የፈተና ወቅት ስለሆነ በፈተና አሰጣጥ ላይ ምንም አይነት ክፍተት እንዳይፈጠር ትምህርት ክፍሎች ላይ የማስተባበር ስራው በተሳካ ሁኔታ እንዲሰራበት ይጠበቃል" በማለት አቅጣጫ ሰጥተዋል::
በመድረኩ የየኮሌጆቹ ዲኖች: የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር: የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር እንዲሁም የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር የግማሽ አመቱን የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ተሳታፊዎች በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ጥያቄያቸውን እያነሱ ነው:: የአስተያየትና ጥያቄውን የውይይት መርሃግብር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንትና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት የሚመሩት ሲሆን መድረኩ እስከ ነገ ግማሽ ቀን ድረስ እንደሚቀጥል ታውቋል::