የክሊኒካል ጥናት በባህላዊ ሕክምና በሚል ርዕስ አውደ-ጥናት ተካሄደ

“የክሊኒካል ጥናት በባህላዊ ሕክምና፡ ለምን እና እንዴት?” በሚል ርዕስ አውደ-ጥናት ተካሄደ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ባህላዊ ሕክምና ጥናት ቡድን ከም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ጋር በመተባባር  “የክሊኒካል ጥናት በባህላዊ ሕክምና፡ ለምን እና እንዴት?” በሚል ርዕስ በሚያዚያ26/2014ዓ.ም በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ አውደ-ጥናት ተካሄደ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ  ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና ሳይንስ ፋካሊቲ ተ/ዲን እና በሲዳማ ባህላዊ ሕክምና ጥናት ዋና ተመራማሪ የሆኑት ረ/ፕ ጌቱ አታሮ እንደተናገሩት የጥናት ቡድኑ በሶስት ዓመት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት በመንደፍ  በባህላዊ ሕክምና ዙሪያ የቴማቲክ ምርምሮችን በሲዳማ ክልል በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ላይ እያካሄደ መሆኑን ገልፀው እየተሰሩ ያሉትን ምርምሮችንም ለመደገፍ  የሚመለከታቸው የሀገር ውስጥና አለም ዓቀፍ ተቋማት የትብብር ፍላጎት እያሳዩ ሲሆን የዛሬውም አውደ ጥናት የትብብሩ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

ረ/ፕ ጌቱ በማስከተልም እንደገለፁት በዛሬው አውደ-ጥናት ከስውዘርላንድ አንቴና ፋውንዴሽን (Antenna Foundation- SWITZERLAND) የባህላዊ ሕክምና ምርምሮችን በተመለከተ አለም አቀፍ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ዶ/ር በርትራንድ ግሬዝ “የክሊኒካል ጥናት በባህላዊ ሕክምና፡ ለምን እና እንዴት?” በሚል ርዕስ በዘርፉ እየሰሩ ላሉ መምህራኖችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ላላቸው የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪና ባለሙያዎች ጥናታቸውን እና ልምዳቸውን በሰፊው ያቀርባሉ  ብለዋል፡፡

ተመራማሪ ዶ/ር በርትራንድ ግሬዝ የጥናት ውጤታቸውን ሲያቀርቡ ባህላዊ ህክምና እና መድኃኒቶች በሳይንሳዊና ክሊኒካል ጥናቶች ከመረጣ እና ማረጋገጥ ጋር ተያይዞ መከተል ስላለባቸው አሰራሮች እንዲሁም በማይጎዳ፣ ውጤታማ፣ ተደራሽ፣ እና ዘላቂ የሚሆኑበትን መንገድ በተመለከተ ሰፊ ዳሰሳዊ ጥናት ካቀረቡ በኃላ  ከተሳታፊዎችም ጥያቄዎችና አስተያያቶች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ዶ/ር በርትራንድም ለወደፊት በዘርፉ የተጀመረውን ግንኙነት ለማጠናከርና ተደራጅተው ለሚቀርቡ  የጥናት ንድፈ- ሃሳቦች በግላቸውም ሆነ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም ከአውደ-ጥናቱ በተጨማሪ በቀጣዩ ቀን በሲዳማ ክልል በተለዩ የምርምር ቦታዎች በመገኘት የተግባር ምልከታ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ ከሕ/ጤ/ሳ፣ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ እንዲሁም ከሌሎች ኮሌጆች የተውጣጡ ተመራማሪዎች፣ መመህራን፣ ባለሙያዎችና መረጃ ሰብሳቢዎች እንደተካፈሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et