ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አራት የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሳነ መምህራን እና መምራኖች ጋር ውይይትና ምክክር ተካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ከሚገኙ አራት ኮሌጆችና የኢፎርማቲክስ ፋካሊቲ በመምህርነት የሙያ ዘርፍ ተምረው በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ አላሙራ፣ አዲስ ከተማ፣ አዳሬ ሚሊኒየም እና ምስራቅ ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ዕጩ መምህራኖች በመሆን የተግባር ልምምድ ለማድረግ ከመውጣታቸው በፊት ከትምህርት ቤቶቹ ርዕሳነ መምህራን እና መምራኖች እንዲሁም ዕጩ መምህራኖቹን ክትትል ከሚያደርጉላቸው የዩኒቨርሲቲው መምህራኖች ጋር የተግባር ልምምዱን ውጤታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ስልቶች ላይ በጋራ ውይይትና ምክክር መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
በትምህርት ኮሌጅ የመምህራን ትምህርት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አክሊሉ ይሁን በተግባር ልምምድ ስርዓትና የምዘና ሂደት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለተሳታፊዎቹ ሲሰጡ እንደተናገሩት ትምህርት ለአንዱ አካል የሚተው ሳይሆን በጋራ የሚሰራ በመሆኑ ሁላችንም ተባብረን በመስራት የትምህርት ጥራትን ማምጣት የሚኖርብን ሲሆን በዚህ ዓመት የምንልካቸው ዕጩ መምህራኖች እንደዚህ ቀደሙ የ1 ዓመት የመምህርነት ኮርስ ብቻ የወሰዱ ሳይሆኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከሚወስዱት የትምህርት ዓይነት ጋር የመምህርነትን ኮርሶች የወሰዱ በመሆናቸው ለተግባር ልምምዱ ወደ እናንተ ሲመጡ ብዙ ተግዳሮቶች እንደማይገጥማቸው እየገለፅኩኝ የዚህ መሰሉ ልምምድ ት/ቤቶች፣ ተማሪዎች፣ ዕጩ መምህራኖች፣ ርዕሳነ መምህሮች እና የሚመዝኑ መምህራኖች የሚያደርጉት የተግባር የማስተማሪያ ዘዴና የመመዘኛ ሂደት ነው፡፡
ተማሪዎቹን የሚልኩት ኮሌጅ ዲኖችና ኃላፊዎች ፕሮግራሙን አስመልክቶ ከ400 መቶ በላይ የሚሆኑ ዕጩ መምህራን ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣ ከማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ፣ ከትምህርት እና ከህግና ገቨርናንስ ኮሌጆች እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኢፎርማቲክስ ፋካሊቲ የክፍል ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደተመረጡት አራት ት/ቤቶች በመሄድ የተግባር ልምምድ የሚያደርጉ ሲሆን በልምምድ ወቅቱም ከዩኒቨርቲው ክትትልና ምዘና የሚያደርጉ መምህራኖች እንደተመደቡ ገልፀው የተግባር ልምምድ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ከትምህርት ቤቶቹ ርዕሳነ መምህራን እና መምራኖች ጋር የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን ታስቦ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙም ተሳታፊዎቹ ዕጩ መምህራን ወደ ትምህርት ቤታችን ሲመጡ ተቀብለን የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ስናደርግ የቆየን ቢሆንም የዚህ መሰሉ የጋራ ውይይት እና ተቀራርቦ መስራት ችግሮች ሲፈጠሩም ተናቦ ለመስራትና መፍትሄ ለማበጀት እንደሚረዳ ገልፀው በቀጣይም የዚህ መሰሉ ፕሮግራም እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡