በሁለት ረቂቅ ሰነዶች ላይ ለመምከር የውይይት መድረክ ተዘጋጀ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው ሁለት ረቂቅ ሰነዶች ላይ ለመምከር የውይይት መድረክ አዘጋጀ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕ/ጽ/ቤት ስር የማህበረሰብ ጉድኝት ረቂቅ ስትራቴጂክ ሰነድ እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ መመስረቻ ሰነድ ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡

የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በመክፈቻው ላይ ዩኒቨርሲቲው በተለይ ባለፉት 22 ዓመታት በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እና ከ11 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተመረጡ ወረዳዎች የቴክኖሎጂ መንደሮችን በማዘጋጀት በግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ስነ-ምግብ እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃዎች ላይ ምርምርና ቴክኖሎጂዎችን የማላመድና የማሸጋገር ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም እንደሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮዎች አንፃር 15 ፐርሰንት ያህሉን  የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እንዲያከናውኑ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ ወረዳዎች እየበዙና ፍላጎታቸውም እየጨመረ በመምጣቱ እስካሁን እንመራበት የነበረውን አካሄድ ወጥና ተደራሽ ለማድረግ መከለስ በማስገለጉ በማህበረሰብ ጉድኝት ረቂቅ ስትራቴጂክ ሰነድ ላይ ተወያይቶ እንደ አዲስ ለማዘጋጀት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ታፈሰ አክለውም በዚሁ መድረክም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ንድፈ ኃሳቦች ያላቸውን መምህራን እና ተመራማሪዎች በመለየት ንድፈ ኃሳቦቻቸውን እና የቴክኖሎጂ  አዳዲስ ፈጠራዎቻቸውን እንዲያጎለብቱ ለመደገፍ፣ ቦታዎችን በመለየት በተግባር እንዲሞክሩበት እንዲሁም ከአዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ሃገራችንን፣ ዩኒቨርሲቲውን እና እራሳቸውን የሚጠቅሙበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ በዩኒቨርሲቲው ለማቋቋም ህጋዊ ሰነድ በማስፈለጉ በመመስረቻ ሰነዱ ላይም በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ  በበኩላቸው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ለመከወን በራሱ ተነሳሽነት ሰነድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲያደግር የቆየ ሲሆን የዚህ መሰሉ ተልዕኮ አንዱ ሰጪ ሌላኛው ደግሞ ተቀባይ በመሆን የሚሰራ ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ አርሶ አደሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ የሚተገብሩት በመሆኑ ሁሉም አካላት በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተወያይቶ ተፈፃሚነቱ ላይም አቅጣጫ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ገልፀው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ መመስረቻ ሰነድም ከዩኒቨርሲቲው የሚፈልቁ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶችና ቴክኖሎጂዎች ለተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ በመሆናቸው ህጋዊ ሰነዱ ላይ በመምከር የዩኒቨርሲቲው ገቢንና አቅምን ለማሳደግ፣ ተመራማሪዎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ እንዲሁም በሀገር በቀል ዕውቀት ችግሮችን ለመፍታትም  ሃገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

በፕሮግራሙም ላይ ሁለቱም ሰነዶች ቀርበው ውይይት እና ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠው ውይይቱ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et